ሰንበት ትምህርት ቤት

ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ። ፪ኛ ጴጥ ፩፡ ፲

የሰንበት ት/ቤት መሠረቱ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እንደነበር ቅዱሳት መጽሐፍት ያስረዳሉ። በኦሪት ዘዳግም "እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሯቸው፣ በአይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁን፣ ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፣ በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድህም ስትሄድ ስትነሳም አጫውታቸው" የሚል እናነባለን። ዘዳ ፩፡ ፮-፱። ይህም እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ሕገ እግዚአብሔር እንዲያስተምሯቸው መታዘዛችውንና፤ በትእዛዙም መሰረት ሕፃናቶቻቸውን በቤተ እግዚአብሔርና በቤታቸው ሕገ ኦሪትን እያስተማሩ ያሳድጓቸው እንደነበር እንገነዘባለን።

ሰንበት ት/ቤት በዘመነ ሐዲስ በ ፪፻ ዓ. ም. በፈረንሳይ ሀገር በፓሪስ ከተማ እንደተጀመረና ከዚያም በአውሮፓ እና ሌሎች አህጉራትም እንደተስፋፋ ይነገራል። በአገራችን በኢትዮጵያም እንደ አሁኑ በዘመናዊ መልክ ባይቋቋምም ቀደም ሲል የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና መምህራን በየቤተ ክርስቲያኑ ደጀ ሰላምና በየዛፉ ስር በየመንደሩም ጭምር ሕጻናትን በመሰብሰብ ያስተምሩት የነበረው የሰንበት ትምህርት ቤት መሰረትና መነሻ መሆኑ ግልጽ ነው። ይህንን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕገ ወንጌልን ለማስፋፋት ከሚያስፈልጓት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የሰንበት ት/ቤትን ማቋቋምና ማደራጀት መሆኑን ተገንዝባ ሰንበት ት/ቤትን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እንዲቋቋም አድርጋለች። ይህንንም ተልዕኮ የሚከታተል የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከጠቅላይ ቤት ክህነት እስክ ወረዳ ቤት ክህነት የሚዘልቅ መዋቅር ዘርግታለች።

በዚህም መሠረት የኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርሰቲያንም የሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም አድርጋለች። የሰ/ት/ቤቱ ዓላማም በመጽሐፈ መክብብ ምዕ ፲፪፡ ፩ ላይ “የጭንቅ ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ሃይለ ቃል አብነት በማድረግ ማንኛውንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኝ የሆነ በፈቃደኝነት እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚመጣውን ወጣት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ስር በመሰብሰብ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲቀስም፣ የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት፣ ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በማወቅ እንዲፈጽም ለማድረግና ፈሪሃ እግዚአብሔር አድሮበት ፈጣሪውን እንዲያመሰግን ለማድረግ ነው። እንዲሁም ቅዱስ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በመዝሙሩ (መዝ ፻፴፪፡ ፩--፫) “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው። በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን አዟልና”ሲል ያስተማረውን በመተግበር ወጣቶችን በማሰባሰብ በረከትን እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

ሰንበት ት/ቤቱ የተቋቋመው ቤተ ክርስቲያናችን ስትመሰረት ጀምሮ ሲሆን በወቅቱም ጥቂት ወጣቶችን በማቀፍ ነበር። ዕለት ከዕለትም እንቅስቃሴው እየሰፋ መጥቶ ት/ቤቱ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል። ሰንበት ት/ቤቱ የተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎችን በስሩ አዋቅሮ አገልግሎትን በመስጠት ላይ ይገኛል። እነዚህም፡

 ጽ/ቤት (ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበርና ጸሐፊን ያካተተ)
 የመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
 የትምሕርት ክፍል
 የአባላት ግንኙነት ክፍል
 የልማትና በጎ አድራጎት ክፍል
 የሕጻናት ትምሕርት ክፍል እና
 የንብረትና ገንዘብ አያያዝ ክፍል ናቸው

ሰንበት ት/ቤቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥቂቶቹ፡
• ዘወትር እሑድ ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ ወቅቱን የተከተሉ መዝሙሮች መዘመር
• በወርኃዊ ቋሚ የሰርክ ጉባዔ ላይ ዕለቱን የተከተሉ መዝሙሮች ማቅረብ
• በዓመታዊ ዓበይትና የንግስ በዓላት ላይ ወረብ፣ መዝሙሮች፣ ስነ ጽሁፍ፣ ኪነጥበብና ጭውውቶች አዘጋጅቶ ማቅረብ (ለዝርዝሩ የፒዲኤፍ ፋይሉን ይጫኑ)
• በአጎራባች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሚከብሩ ዓመታዊ የንግስ በዓላት ላይ መገኘትና ማክበር
• ታዳጊ ሕጻናት በመንፈሳዊ ህይወት ተኮትኩተው እንዲያድጉ በማስተማሩ ስራ ላይ መሳተፍ
• የቤተ ክርስቲያን ህንጻ አሰሪ ኮሚቴ በሚያዘጋጃቸው ልዩ ልዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐግብሮች ላይ መሳተፍ
• ካህናትንና መምህራንን ከሌሎች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመጋበዝ ምዕመኑን ወንጌል እንዲያስተምሩ ማድረግ ናቸው

በመጨረሻም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልእክቱ ምዕ ፫ ቁ ፲፫ “በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማነው” ባለው መሠረት ቅድስት ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን በተቻላችሁ መጠን ለማገልገልና ለመሳተፍ፣ ቃለ እግዚአብሔር ለመማርና መንፈሳዊ ሕይወታችሁን ለማጎልበት የምትፈልጉ በአጥቢያችን የምትገኙ ወጣቶች በሙሉ ይህንን የአባልነት መመዝገቢያ ቅጽ ሞልታችሁ ለጽ/ቤት በማስገባት የሰንበት ት/ቤቱ አባል መሆን እንደምትችሉ እንገልጻለን።

Download sunday school membership form from here

እግዚአብሔር አገልግሎታችንን ይባርክ!